በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት (DARS) የውክልና ሥልጣን (Power of Attorney) እንዴት መስጠት ይቻላል?
ለአንድ ሰው የውክልና ሥልጣን መስጠት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ሕጋዊ ተግባር ነው። በፌዴራል ደረጃ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት (DARS) ውክልናን የማፅደቅ እና የመመዝገብን ስራ በማከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን በክልሎች ይኸው ተግባር በፍትህ ቢሮዎች እና የዐቃቤሕግ ቢሮዎች ይሰራል። በፌዴራል ደረጃ በተለይም በአዲስ አበባ የሰነዶች ማረጋገጫ ፅ/ቤት አሠራሩን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል የቀየረ በመሆኑ፣ አሁን ላይ የውክልና ሰነዶችን በበይነመረብ (Online) ማዘጋጀትና ቀጠሮ መያዝ ግዴታ ሆኗል። ይህን ሒደት ያለ ምንም እንግልትና ስህተት እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ደረጃ በደረጃ እንመልከት።
1ኛ፡ ወደ ድረ-ገጹ መግባት፣ የውክልና አይነት መምረጥ እና የወካይን መረጃ መሙላት
የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ማንኛውንም አገልግሎት ለመስጠት የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያን (Fayda ID) መጠቀምን ግዴታ አድርጓል።
- በመጀመሪያ በኮምፒውተርዎ ወደ dars.gov.et ድረ-ገጽ ይግቡ።
- የሚሰጡትን የውክልና አይነት ይምረጡ፤ ጠቅላላ ውክልና፣ ልዩ ውክልና፣ የቤተሰብ ውክልና እና የጠበቃ ውክልና አይነቶች ምርጫ በድረገፁ ግራ ክፍል ስለሚያገኙ የፈለጉትን አይነት ይምረጡ።
- ውክልና ሰጪው (Principal) በዲጂታል መታወቂያው ላይ ያለውን የFAN ቁጥር (Fayda Account Number) ያስገባል።
- በመቀጠል መታወቂያው በሚወጣበት ጊዜ ከተመዘገበው የስልክ ቁጥር ጋር የተያያዘ የአንድ ጊዜ ሚስጥራዊ ቁጥር (OTP) ወደ ስልኩ ይላካል። ይህንን የኦቲፒ (OTP) ቁጥር በማስገባት ማንነትዎን ያረጋግጡ።
2ኛ፡ የወኪሉን (Agent) መረጃ ማስገባት እና ስልጣኖችን መምረጥ
ለውክልና ሰጪው የተደረገው ተመሳሳይ የይለፍ ቃል ማረጋገጫ ሒደት ለወኪሉም (ውክልና ለሚቀበለው ሰው) ያስፈልጋል።
- የወኪሉን መረጃ እራስዎ በእጅዎ (Manually) ማስገባት ይችላሉ፤ ወይም የወኪሉን የFAN ቁጥር በማስገባት እና ወደ ወኪሉ ስልክ የሚላከውን OTP በመጠቀም መረጃውን በቀጥታ ከብሔራዊ መታወቂያ ቋት (Database) መሳብ ይቻላል።
- የጠበቃ ውክልና በሚሆንበት ጊዜ የባለሙያው ሙሉ ስም፣ አድራሻ እና የጥብቅና ፈቃድ ቁጥር ስለሚያስፈልግ ይህንኑ መረጃ ማስገባትዎን እንዳይዘነጉ።
- ወካይ እና ወኪልን የሚመለከቱ መረጃዎች በፋይዳ ቁጥር አማካኝነት ሲሞሉ ከብሔራዊ መታወቂያ ማዕከል በቀጥታ የሚመጡ ቢሆንም፣ አንዳንድ ያልተሟሉ ዝርዝሮችን እራስዎ ማስተካከልና ማሟላት ይኖርብዎታል።
- በመቀጠል ወኪሉ እንዲኖረው የሚፈልጉትን የውክልና ሥልጣን ወሰን (Powers) በጥንቃቄ ይምረጡ። በተጨማሪ በግልፅ ተለይተው ሊሰጡ የሚገባቸው ስልጣኖች ካሉ ተጨማሪ ስልጣን የሚለውን በመንካት በፅሁፍ ማስገባት ይቻላል።
- በውክልና ሰነዱ ላይ ንብረቶችን መጥቀስ ካስፈለገ ለምሳሌ ያህል መኖርያ ቤት፣ ንግድ ድርጅት፣ መኪና ወ.ዘ.ተ፣ የመብት ማረጋገጫ ማስረጃው መቅረብ የሚኖርበት ሲሆን ንብረቱን የሚመለከቱ አስፈላጊ ዝርዝር መረጃዎችን በጥንቃቄ ማስገባት ያስፈልጋል።
- ውክልናው ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እንዲቆይ ከፈለጉ መቼ እንደሚያበቃ ቀኑን ለይተው መግለፅ የሚችሉ ሲሆን፣ እስከሚሻር ድረስ አገልግሎት እንዲሰጥ ከፈለጉ ላልተወሰነ ጊዜ ውክልናውን መስጠት ይችላሉ።
3ኛ፡ ረቂቁን ማረጋገጥ እና ማተም
- መረጃዎቹ ተሞልተው ሲያልቁ የውክልና ሰነዱን ናሙና (Sample) ያሳየዎታል።
- በሰነዱ ላይ ያሉ ስሞች፣ አድራሻዎች እና የተሰጡት የሥልጣን ዓይነቶች ሙሉ በሙሉ ትክክል መሆናቸውን በደንብ ያረጋግጡ።
- ሁሉንም ካረጋገጡ በኋላ ሰነዱን ያትሙ (Print)።
4ኛ፡ በqetero.com የቀጠሮ ጊዜ መያዝ እና ክፍያ መፈጸም
- ወደ qetero.com በመግባት ስልክ ቁጥሮን በማስገባት የሚላክሎትን OTP ተጠቅመው ይግቡ።
- ተቋም ይምረጡ የሚለው ላይ የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎትን በመምረጥ ቅርንጫፍ ይምረጡ።
- የአገልግሎት ጠያቂ ስልክ እንዲያስገቡ ይጠየቃሉ፤ በዚህ ደረጃ የወካይን ስልክ መጠቀም የግድ ነው።
- አገልግሎቶች በሚል ምርጫ ውክልና የሚለውን ይምረጡ እና በቅርንጫፉ ለአገልግሎት ክፍት ከሆኑ ሰዓቶች ለዕርሶ የሚያመቾትን ይምረጡ።
- ቀጠሮው የሚያዘው ለሌላ ሰው ከሆነ የወካዩ ስልክ ቁጥርን የግድ አስገብቶ የሚላከውን OTP ማስገባት አስፈላጊ ነው።
- በqetero.com አማካኝነት በአንድ ጊዜ እስከ 3 ለሚደርሱ የውክልና ሰነዶች ለሰነድ ማረጋገጫ ቀጠሮ ለመያዝ የ50 ብር ክፍያ የሚጠየቅ ሲሆን ይህንን በቴሌብር እንደከፈሉ የቀጠሮ ማረጋገጫ መልዕክት ይደርሶታል።
ይህንን ዲጂታል አሠራር መከተልዎ ጊዜዎን ከመቆጠቡም በላይ ሕጋዊ ጉዳይዎን ያለ ምንም እንግልት ለማስፈጸም ይረዳዎታል። ስለ ውክልና ሕጋዊ ውጤቶች እና የሥልጣን ወሰን ተጨማሪ ማብራሪያዎች ካስፈለግዎት የlawyer.et የሕግ ባለሙያዎችን ማማከር ይችላሉ።
Need Professional Legal Guidance?
Our team is ready to assist you with complex power of attorney drafting and legal due diligence.
Schedule Consultation