በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ የመኖሪያ ሕንፃ እና የመሬት ይዞታ
በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ይዞታ እና የሕንፃ ግንባታ ገጽታ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት አጠቃቀም መብት የሚተላለፈው በሊዝ ሥርዓት አማካይነት ሲሆን፤ አፈጻጸሙም በጨረታ ወይም በምደባ ይከናወናል።

በከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 መሠረት “የሊዝ ይዞታ” ማለት በጊዜ በተገደበ የውል ስምምነት የከተማ ቦታን የመጠቀም መብት የሚገኝበት የመሬት ይዞታ ስሪት ነው። በሌላ በኩል “ነባር ይዞታ” የሚባለው የከተማ ቦታ በሊዝ ሥርዓት መተዳደር ከመጀመሩ በፊት በሕጋዊ መንገድ የተያዘን ወይም የሊዝ ሥርዓቱ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ለነባር ይዞታ ተነሺ በምትክ የተሰጠን ቦታ ያጠቃልላል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሻሻለው የከተማ መሬት ሊዝ ደንብ ቁጥር 162/2016 የሊዝ አዋጁን አፈጻጸም የተመለከቱ ዝርዝር ድንጋጌዎችን ያካተተ ሲሆን፤ አዋጁ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ከመንግሥት ለባለይዞታዎች የሚተላለፉ ማናቸውም ቦታዎች በሊዝ ሥርዓት—ማለትም በጨረታ ወይም በምደባ—እንዲተላለፉ በሕጉ ተደንግጓል።

ነባር ይዞታ ወደ ሊዝ ሥርዓት የሚገባባቸው ሁኔታዎች

  • በውል የሚደረግ ዝውውር፦ ነባር ይዞታ በሽያጭ ወይም በስጦታ ለሦስተኛ ወገን ሲተላለፍ በቀጥታ ወደ ሊዝ ሥርዓት እንዲገባ ይደረጋል። በዚህም መሠረት ተረካቢው (ገዢ ወይም ስጦታ ተቀባይ) ከሚመለከተው የአስተዳደር አካል ጋር የሊዝ ውል በመፈረም ተገቢውን የሊዝ ክፍያ የመፈጸም ግዴታ አለበት።
  • ይዞታን ማቀላቀል፦ አንድ ባለመብት በነባር ይዞታነት እና በሊዝ ስሪት የሚተዳደሩ ይዞታዎችን እንዲቀላቀሉለት ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ሲያገኝ፣ ነባሩ ይዞታ ተጠቃሎ ወደ ሊዝ ሥርዓት እንዲገባ ይደረጋል።

በነባር ይዞታነት የሚቀጥሉ ልዩ ሁኔታዎች

ሕጉ በተለየ ሁኔታ የሚከተሉትን ዝውውሮች ከሊዝ ሥርዓት ውጭ በማድረግ በነባር ይዞታነት እንዲቀጥሉ ይፈቅዳል፦

  1. የውርስ ዝውውር፦ የነባር ይዞታ ባለመብት ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ እና ይዞታው በሕጋዊ መንገድ ለወራሾች ሲተላለፍ፤
  2. የጋብቻ ንብረት ክፍፍል፦ የባልና ሚስት የጋራ ሀብት የነበረ ነባር ይዞታ በስምምነትም ሆነ በፍርድ ቤት ውሳኔ ተሸንሽኖ ሲከፋፈል ወይም ለአንደኛው ወገን ድርሻ ሆኖ እንዲቀር ሲደረግ።

የመሬት ይዞታ ዝውውርን በሚመለከት የሕግ አገልግሎት ያስፈልጎታል?

የሕግ ቢሯችን በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ማረጋገጥ፣ የካርታ ትክክለኛነት ፍተሻ እና ውሎችን የማዘጋጀት የተሟላ ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣል።

ቀጠሮ ይያዙና ያማክሩ